ውሽት ነገሠ!
መስቀል አደባባይ- ሀዝባችን ተጠርቶ
ሕጻን ሽማግሌው ባልቴት እና አዋቂው-
ግልብጥ ብሎ ወጥቶ
የክብር እንግዶች- ከአውሮጳ ከእስያ
ከጎረቤት ሃገር- ጅቡቲ ኬንያ
የአማሪካው ቆንሲል- ሚስተርም ተገኝተው
ጳጳሱ ተጠርተው- ካህናት ቀድሰው
ቅባ-ቅዱስ ፈልቶ-በአናቱም አፍስሰው
አክሊል ተደፋለት- እምቢልታ ተነፋ
ሕዝብ ሠገደለት- ሥልጣን ክብሩ ሰፋ
ከበሮ ተመታ-ሆታውም ቀለጠ- እልልታ ተሰማ
ውሸት ንጉሥ ሆነ- ሰርቆት አልጋ ወራሽ-በአገሬ ከተማ።
እናም የእኛ ሰፈር- ትልቅ ሽማግሌ
አንቱ የተባሉት- ትናንት እና ዛሬ
በቁርባን ያገቡት- በክርስትናቸው
ይኸው በአደባባይ -ሲዋሹ ያዝናቸው።
መቸ ይኸ ብቻ- ሆነና ነገሩ
በሃሰት ተከስው- ተሰማና ፋይሉ
ደግነት ቅንነት- እስር ቤት ገቡ አሉ።
እንግዲህ ምን ይሉ- ዘመን ተቀየረ
ውሃ ሽቅብ አይፈስ- ሲባልም ነበረ
ዘመን ተገላብጦ - ውሸት ተከበረ።
ኑሯችን ሆነና- ከደሃው ቀምተን
እውነትን ንቀነው- ውሸትን አንግሰን
ወደፊት ለመሄድ - መራመድ አቃተን።
ዳግማዊ ዳዊት
የካቲት 2002 ዓ.ም.